ብሄራዊ የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ 02/03/2014(ንቀትሚ) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በብሄራዊ የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን ረቂቅ ስትራቴጂ ዙሪያ ህዳር 1/2014 ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ባለፉት አምስት ዓመታት ሃገሪቱ ወደ ውጪ ከላከቻቸው ምርቶች የተገኘው ገቢ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ያልዘለለ መሆኑነን ጠቅሰው በ2013 በጀት ዓመት በተቋማት መካከል በተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር ምክንያት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 3.64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳን ይህ የውጪ ምንዛሬ ግኝት መልካም ቢባልም የኤክስፖርት ግኝታችንን ለማሳደግ የወጪ ንግድ ምርቶች ስብጥር አነስተኛ መሆን፣ ህገወጥ ንግድ፣ ለጥሬ ዕቃ ግዢ የሚያስፈልግ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ ሃገሪቱ ካላት ዕምቅ ሃብት አንጻር የንግድ ሚዛናችንን አለመመጣጠን እንዲሁም የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አለመሳተፋቸው እንደ ትልቅ ተግዳሮት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሾች መሆናቸውን ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
ነባር ምርቶች ላይ ልዩ አትኩሮት ከመስጠት በተጓዳኝ አዳዲስ ምርቶችን በመለየት ወደ ውጪ ገበያ ማስገባት እና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት በቀጣይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸው አበይት ጉዳዮች እንደሆኑም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ይህ በሂደት ላይ ያለው የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን ረቂቅ ስትራቴጂ በቀጣይ የኤክስፖርት ግኝትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሩ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ሲገባ ሁሉም የሚኒስቴር መ/ቤቱ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለድርሻ የሆኑ ሚኒስትሮች እና በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

Share this Post