“ችግር ፈቺ የአገርና የዜጎችን ተስፋ የሚያለመልም የወደፊቱን ማየት የሚችልና እና በተለይም ዘርፉን ወደ ፊት የሚያሻግር ቁርጠኛ አመራር ይጠይቃል”

አዲስ አበባ 06/03/2014 ዓ.ም (ኢሚ) አገራችን የገጠማትን አሁናዊ ፈተናዎች አልፋ የተሻለ ምዕራፍ ላይ እንድትገኝ ቁርጠኛ አመራር  ያስፈልጋል፤አሁን ያለንበት ጊዜ ብዙ ተስፋዎችና ፈታኝ ሁኔታዎች ያሉበት ቢሆንም እነዚህን ተስፋዎች ለመጠቀም የገጠሙንን ፈተናዎች ለማለፍ ጠንካራ አመራር ይጠይቃል ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ ለየት ባለ መንገድ ችግር የሚፈታ፣ የአገርና የዜጎችን ተስፋ የሚያለመልም የአሁኑን ብቻ ሣይሆን የወደፊቱን የሚያይ ቁርጠኛ አመራር በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ወደ ፊት ሊያሻግር የሚችል አመራር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከክልሎችና ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት ጋር የ2014 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ስራ ሪፖርት የግምገማ ባደረጉት መድረክ አገራችን የገጠማት ፈተናዎች ሌሎች አገራት ገጥሟቸው እንደነበርና ያንን ፈታኝ ጊዜ ተቋቁመው አሁን ላሉበት ስኬት መብቃታቸውን ለአብነት ያነሱት አቶ መላኩ እኛም ከዚህ አይነቱ ችግሮች ለመለወጥ እርግጠኞች እና ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን ማድረግ የሚቻለው አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም የህግ የበላይነት ማስፈን ሲቻል እንደሆነም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣትም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ ስራዎች መስራት የግድ ነው ያሉት አቶ መላኩ የህልውና ጦርነቱ በየትኛውም ውጤት ቢጠናቀቅ ያንን የሚሸከም አስተማማኝ ኢኮኖሚ ከሌለ እና ለዜጎች የስራ ዕድል ካልተፈጠረ ሌላ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የምንዳረግ በመሆኑ በዘርፉ የሚሰሩ ስራዎች የአገር ሉአላዊነት ለማስከበር ከሚሰራው ስራ ተለይቶ ሊወሰድ የሚችል አይደለም ሲሉ አጽዕኖት ሰጥተዋል፡፡

Share this Post