የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ከክልልና ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ጋር የአፈጻጸም ግምገማ አካሄደ

አዲስ አበባ 06/03/2014 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማቱ እና ከክልልና ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር የ2014 በጀት የመጀመሪያ ሩብ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል፡፡
አሁን  ያለንበት ወቅት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵዊነትን ለማጥፋት የውጭና የውስጥ ኃይሎች በቅንጅት የከፈቱብንን ጦርነት ለመመከትና የአገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ እንዲሁም አገራችንን ለማገልገልና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምንለፋበት  ወቅት  ነው ያሉት የመሰረተ ልማትና ግብአት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሺሰማ ገ/ሥላሴ የጀመርነውን ሀገራዊ ለውጥና ማሻሻያ ለማሳካት የምንታትርበት ወቅት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ተገደን የገባንበት የህልውና ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት፣ የደረሰብንን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኦኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም እና የወደሙ መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት በግብርና ኢንዲስትሪ እና በሁሉም አገልግሎት ዘርፎች ከጦርነቱ ያልተናነሰ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል  ያሉት አቶ ሺሰማ መንግስትም ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጦ  በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  
በተደረጉ ጥረቶችም በአገራችን የግብርና ዘርፍ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ  የምንችልበት ሁኔታዎች ላይ እንደምንገኝ ግንዛቤ ተውስዷል ያሉት ሚኒስትሩ በአንጻሩ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በርካታ ማነቆዎች የተደቀኑበት በመሆኑ ፈጣንና ጊዜ የማይሰጡ ችግሮችን እየፈታን በተቀናጀ መልኩ ማቀድና መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ልማት ምንነትና ታሪካዊ ዳራ፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የ2014 በጀት አመት ዕቅድ እና በአዲሱ አዋጅ መሰረት የሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት ስልጣን እንዲሁም የክልሎች አደረጃጀት ምን መምሰል አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

Share this Post