የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተከበረ

አዲስ አበባ 29/03/2014 ዓ.ም (ንቀትሚ) የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ኢኮኖሚውን የጎዳውን የህውሃት አገዛዝ ህዝቡ በአንድነት ታግሎ በመጣል ለእውነተኛ የፌደራል ስርአት መዘርጋት የድርሻውን እየተወጣ ባለበት ወቅት መከበሩ ለይት ያደርገዋል ሲሉየንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር  አቶ ገ/መስቀል ጫላ ተናገሩ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራና ሰራተኞች 16ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን “ወንድማማችነት ለህብረብሔራዊ እንድነት” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡
በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሮችና ህዝቦች በህገ-መንግስት ሉአላዊነታቸውን ያረጋገጡበት ነው ያሉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስተሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ የዘንድሮ በዓል ለየት የሚያደርገው ላለፉት 27 አመታት በብሄር ብሔረሰቦች እና በህብረ ብሔራዊነት ሽፋን የአንድ ብሔር የበላይነት የገነነበት በይበልጥ ኢኮኖሚውን የጎዳውን የህውሃት አገዛዝ ህዝቡ በአንድነት ታግሎ ከጫንቃው ላይ አውርዶ በመጣል ለእውነተኛ የፌደራል ስርአት መዘርጋት የድርሻውን እየተወጣ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የበዓሉ መከበር የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ አጠናክሮ ማስቀጠል እና ስለ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የፌደራሊዝም ስርአት ግንዛቤ የማስጨበጥ አላማ እንዳለው የጠቀሱት ሚኒስትሩ በህልውና ትግሉ አገራችን ተገዳ የገባችበትን ጦርነት አጠናቃ ሙሉ አቅሟን ወደ ሰላምና ኢኮኖሚ ግንባታ እስክትደርስ ድረስ የእኛ ተሳትፎ ያስፈልጋታል ያሉ ሲሆን  የተሰማርንበት ዘርፍ ብዙ ሃብት የሚንቀሳቀስበት ቅንነት፣ ሃቀኝነት እና በርካታ ውሳኔን የሚፈልግ በመሆኑ በቀጥታ ከሚደረገው ውጊያ ያልተናነሰ ትግል የሚደረግበት መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት  የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ከቀድሞ በተለየ ሁኔታ ልንታገል ይገባል ብለዋል፡፡
እለቱን አስመልክቶ የአገርን ህልውና በማስከበር የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ህዝቦች ያላቸው ሚና እና የፌደራሊዝም ስርአትና ምንነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

Share this Post