ጥሩ የሰራ ሠራተኛ የሚበረታታበት ለተገልጋይ ክብር የማይሰጥ ሠራተኛ እርምጃ የሚወሰድበት አሰራር ይዘረጋል

አዲስ አበባ፣20/5/2014 (ንቀትሚ) ሚኒስቴር መ/ቤቱ ያለፉትን የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እንዲሁም በቀጣይ 6 ወራት በሚሰሩ ቁልፍ እና አበይት ተግባራት ዙሪያ ከመስሪያ ቤቱ የስራ ክፍል ሃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

 ይህንን  የውይይት መድረክ  በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት   የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር  ክቡር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ  ናቸው፡፡ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው  ባለፉት 6 ወራት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የተቀናጀ ርብርብ አበረታች ውጤት መመዝገቡን እና በዚሁም  ባለፉት  ስድስት ወራት  1.981 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ  1.891 ቢሊየን  የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ የወጪ ንግዱ የእቅዱን 95% የተከናወነ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 322 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም 20.55% እድገት  ማሳየቱንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተመዘገበው ውጤት ሃገራችን ካለችበት ዘርፈ-ብዙ ችግር   አኳያ ሲታይ የሚያኩራራ እንዳልሆነም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

 ባለፉት 6 ወራት ከሪፎርሞች በመነሳት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ከተሰሩ ስራዎች ውስጥም በሃገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋመው ግብረ-ሃይል በመታገዝ በበዓላት ወቅት እና የግብይት ችግር ባሉባቸው ጊዚያት በተደረገው  የገበያ ክትትል በአንጻራዊነት በመሠረታዊ ሸቀጦችና እና ምግቦች ላይ አንጻራዊ የዋጋ ቅናሽ መታየቱ፣ በነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች ዙሪያ ሪፎርሞችን ለማከነወን የሚያስችል ጥናት በማድረግ የነዳጅ ዋጋ ግንባታ፣ የትርፍ ህዳግ እና የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካካያ እና የድጎማ አፈጻጸም ውሳኔዎችን በማጸደቅ በቀጣይ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን፣ እንዲሁም የወጪ ንግድ ስራዎችን ለማሳለጥና ወጤታማ ለማድረግ   የወጪ ንግድ ልማትና ፕሮሞሽን ስትራቴጂ፣የቁም እንሰሳት ግብይት ረቂቅ ፖሊሲ፣ የንግድ ፖሊሲ ስራም  እየተፋጠነ መሆኑ እንዲሁም በ2003 የወጣው የዕቃ ማከመቻ ደረሰኝ ስርዓት መመሪያ ተዘጋጅቶለት ተግባራዊ መደረጉ  ተጠቃሾች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በ6 ወራት የተመዘገቡት ውጤቶች በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ያሉት አቶ ገ/መስቀል በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት የሁለቱ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ህንጻ ሳይለይ በአንድ ቦታ መሆኑ እንደ ትልቅ ተግዳሮት ከሚነሱ ችግሮች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህንንም ትልቅ ተግዳሮት ለመቅረፍ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የራሱ ህንጻ እንዲኖረው በተደረገው ጥረት ቀድሞ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሲጠቀምበት የነበረውን ህንጻ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ምክክር ተደርጎ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኤርጎኖሞክስ ጽንሰ ሃሳብን መሠረት በማድረግ የዕድሳት ስራውን ለማድረግ የዲዛይን ጥናቱ ተጠናቆ በግዢ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ምቹ የስራ አካባቢን ከመፍጠር አንጻር ሚናው የጎላ እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን አጠናክሮ መቀጠል፣ በህገ ወጥ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃዎችን መውሰድ፣ በግብይት ሂደቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እና ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን መቅረፍ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ተግባራት መሆናቸውን አቶ ገ/መስቀል ጠቁመዋል፡፡

 ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ስራ መሳካት የሁሉም ሠራተኞች ሚና የላቀ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህም መሰረት ማንኛውም ፈጻሚ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ዕቅድ የራሱ ዕቅድ መሆኑን በአግባቡ ሊረዳ እንደሚገባና የተሰጠውን ሃላፊነት በመልካም ዲሲፒሊን መወጣት እንዳለበት ይህ ካልሆነ ግን ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራርም መዘርጋቱን ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ 6 ወራት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንዲቻል ሁሉም ሠራተኛ ማንኛውም ተገልጋይ አገልግሎት ፈልጎ ሲመጣ "ደንበኛ ንጉስ ነው" በሚል መርህ በታላቅ ትህትና እና በፍቅር ማስተናገድና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባው ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ ጥሩ የሰራ ሠራተኛ የሚበረታታበት በተቃራኒው ለተገልጋይ ክብር የማይሰጥ ሠራተኛ ካለ እርምጃ የሚወሰድበት አሰራር እንደሚዘረጋም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ የቀጣይ 6 ወራት እቅድ እና አዲሱ አደረጃጀት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

 

Share this Post