በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፣ 10/6/2014 (ንቀትሚ) ብሔራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ለመፍጠር እንዲሁም በአገር ውስጥ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት ብቁ በሆነ የሰው ሃብትና አስፈላጊ በሆኑ መሰረተ ልማቶች የተደራጁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ተናግረዋል፡፡

በአገር ደረጃ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳሰቀሰ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እና በአለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድር ሂደቶች እየተሳተፈች ቢሆንም ከጥራትና መሠረተ ልማት ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ እንዳለው የግል ዘርፉ በአለም ተዋዳዳሪ እንዳይሆን ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል አንዱ ጥራት በመሆኑ እነዚህን ችግሮች የሚፈታ የጥራት ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እየተዘጋጀ ላለው የጥራት ፖሊሲ መጠናቀቅና ተግባራዊነት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡  

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተዘጋጀው የጥራት ፖሊሰ ረቂቅ ላይ በዛሬው እለት ከባለድርሻዎች ጋር ምክክር እያደረገ ይገኛል፡፡

Share this Post