የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ100 ቀናት ዕቅድ

አዲስ አበባ 19/02/2014 (ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በስድስት ስትራቴጂክ የውጤት መስኮች ላይ ያተኮረ የቀጣይ 100 ቀናት እቅድ መሰረት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ከቀድሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተለይቶ በአዲስ የተቋቋመው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያለፉትን አመታት የልማት ዕቅድ አተገባበር፣ የታዩ ክፍተቶችን እንዲሁም የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን ከግምት በማስገባትና ከአስር ዓመቱ የልማት መሪ ዕቅድ በመነሳት የ2014 በጀት ዓመት የልማት ዕቅድ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን፣ ዒላማዎችንና የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚረዱ የማስፈጸሚያ ስልቶችን ያካተተ ዕቅድ አዘጋጅቷል፡፡
የ100 ቀናት ዕቅዱ የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ፣ ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርአት የሚገቡ ወጪ ምርት አይነቶችን ማሳደግ፣ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋፋት፣ የምርትና አገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ፣ የህግ ማዕቀፎችን እና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማጠናቀቅና ማጸደቅ በሚሉ ስትራቴጂክ የውጤት መስኮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በአዲስ መልክ መቋቋም ተከትሎ በርካታ የአደረጃጀትና የለውጥ ስራዎች ለማከናወን በዕቅድ የተያዘ ሲሆን ለግቦቹ መሣካትም የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግበት በእቅዱ ተመላክቷል፡፡
ህገ-ውጥ እና ኮንትሮባንድ ንግድን መከላከል፣ ያአለአግባብ የሚከሰት የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነትን ለመግታት የሚያስችል የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትን ማሳደግ፣ የግብይት ሥርዓቱን በማዛባት በተጠቃሚው ህብረተሰብ ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ ኃይሎችን በመለየት ተጠያቂ የሚሆኑበትን የአሰራ ስርአት መዘርጋት እና የንግድ ግንኙነቶችና ድርድሮችን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ በቀጣይ ትኩረት ያሻቸዋል በሚል በእቅዱ ውስጥ ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል፡፡

Share this Post