የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ 6 ወራት ዕቅድ

አዲስ አበባ፣30/05/2014 (ንቀትሚ) በሃገራችን የተደረገውን 6ኛ ሃገራዊ ምርጫ ተከትሎ በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 በአዲስ መልኩ እንዲዋቀሩ ከተደረጉ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ውስጥ አንዱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱም ከተሰጡት ተግባራትና ሃላፊነቶች ውስጥ የሃገር ውስጥና የውጪ ንግድ ስርዓትን ማሻሻል፣ የጥራት መሠረት ልማትን ማረጋገጥ፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስጣንና የምርት ገበያ ባለስልጣን መ/ቤቶችን ተግባራትና ሃላፊነቶችን አቀናጅቶ መምራት የሚሉት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ እነዚህን በአዋጅ የተሰጡትን ተግባርና ሃላፊነቶች  ለመወጣት ባለፉት 6  ወራት በእቅድ ይዞ ያከናወናቸውን  አፈፃጸሞች አስመልክቶ እንዲሁም በቀጣይ 6 ወራት ስለሚከናወኑ አበይት  ተግባራት   የመስሪያ ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች ውይይት አካሂደዋል፡፡  በውይይት መድረኩ ላይ ባለፉት 6 ወራት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል  የሪፎርም ስራዎችን መሠረት በማድረግ የሃገር ውስጥ ግብይትን  ከስርዓት አልበኝነት ለመታደግ  ጥረት መደረጉ፣ የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች ሪፎርምን ለማከናወን የሚያስችል  ጥናት መካሄዱ፣ የውጪ ንግድ ልማትና ፕሮሞሽን ስትራቲጂ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱ ፣ የቁም እንሰሳት  ግብይት እና   የንግድ ፖሊሲ እየተዘጋጅ መሆኑ፣ በ2003 የወጣውና የሃገር ውስጥ ንግድን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና ያለው የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ፣  ተቋማዊ አደረጃጀትና የለውጥ ስራዎች ክንውን፣ የጫት ምርት ግብይት ጥናት፣ የፓልም የምግብ ዘይት የዋጋ ግንባታ ማስፈጸሚያ የመመሪያ ዝግጅት፣ የእሁድ ገበያ ማስፈፀሚያ ማኑዋል ዝግጅት  ቁልፍ ተግባራት ሆነው ቀርበዋል፡፡

 በግማሽ ዓመቱ 1.981 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ 1.891 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ በማግኘት የእቅዱን 95 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡

ምንም እንኳን በ6 ወሩ የወጪ ንግድ ግኝቱ መልካም የሚባል አፈጻጸም ቢያሳይም በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸው በውይይቱ ላይ ተመላክቷል፡፡ ከታዩ ተግዳሮቶች ውስጥ የቁም እንሰሳት በዝቅተኛ ዋጋ መሸጥ/ under invoice/ እና የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት፣ የአጎዋ የገበያ እድል ስጋት መሆኑ፣የውጭ ሚዲያዎች በሚያስተላልፉት የተዛባ መረጃዎች ገዢዎች የገቡትን  ውል የማቋረጥ ድርጊቶች መበራከት፣ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በመስፋፋቱ ምክንያት ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን በገበያ ላይ መገኝት፣ በየቦታው የተቋቋሙ ኬላዎች ለሸቀጦች ነጻ ዝውውር መሰናክል መሆናቸው የሚሉት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ እንደተናገሩት ምንም እንኳን ከላይ የተዘረዘሩት ተግዳሮቶች ዘርፉን ክፉኛ ቢፈታተኑትም ለቀጣይ ስራዎች ትልቅ ስንቅ የሚሆኑ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገው ቅንጅታዊ አሰራር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የተመዘገበው ውጤት አሁን ሃገራችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሚያኩራራ እንዳልሆነ ሚኒስትሩ   አያይዘው ተናግረዋል፡፡

በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የሚኒስትር መ/ቤቱ የቀጣይ 6 ወራት እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይሰራሉ ተብሎ በእቅዱ ከተካተቱ አበይት ተግባራት መካከል የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ ዘመናዊና ተደራሽ የንግድ አሠራርን ማስፈን፣ የወጪ ንግድን  ማስፋፋት፣ ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ማጠናከር፣ የጥራት መሰረተ ልማትን ማጠናከር እና ጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን የሚሉት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

 

ሚኒስትሩ በቀጣይ ስለሚሰሩ ተግባራት የስራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት ማንኛውም ሠራተኛ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት በጥሩ ዲሲፒሊን መወጣት ይገባዋል ይህ ካልሆነ ግን ተጠያቂነት ይኖራል ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተጣለበት ሃገራዊ ተልዕኮ አንጻር በቀጣይ መሰራት ያለባቸው በርካታ የቤት ስራዎች አሉ፡፡ ይህንን የቤት ስራ በአግባቡ መስራት የሚቻለው እያንዳንዱ ሠራተኛ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ዕቅድ የራሱ ዕቅድ መሆኑን ግንዛቤ ሲኖረው ብቻ ነው እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፡፡ ማንኛውም ሠራተኛ ደመወዝ የሚከፍለው አገልግሎት ፈልጎ ቢሮ የሚመጣው ተገልጋይ መሆኑን በመገንዘብ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት በመስጠት ሃገራዊ  ግዴታውን እንዲወጣ  ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

Share this Post